Ultrafast በOpenAI የብልሽት ምርመራ ጊዜን ከሰዓታት ወደ ደቂቃዎች እንዴት ቀነሰ
ይህ፣ OpenAI የራሱን ቴክኖሎጂና APIዎች እንዴት እንደሚጠቀም የሚያሳዩ ውስጣዊ ምሳሌዎችን ከምናጋራበት ተከታታይ ዝግጅት አካል ነው። እነዚህ መሣሪያዎች በOpenAI ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋሉ ሲሆን፣ ግንባር ቀደም AI በተለያዩ ቡድኖቻችን ውስጥ ሥራዎችን እንዴት እንደሚደግፍ ለማሳየት እዚህ በምሳሌነት ቀርበዋል።
Ultrafast በCodex ውስጥ ያለ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ሁነታ ሲሆን፣ የOpenAI መሐንዲሶች ለብልሽቶች ምላሽ ሲሰጡ የመጀመሪያ ምርጫቸው ሆኗል። አንድ ነገር ሲበላሽ፣ ችግሩ እየተባባሰ እያለ መሐንዲሶች ምላሽ ለማግኘት ለደቂቃዎች የሚጠብቁበት ጊዜ ብዙውን ጊዜ አይኖራቸውም። በUltrafast፣ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ መንስኤዎችን በአንድ ጊዜ መመርመርና ትኩረታቸውን ሳይከፋፍሉ መልሶችን ማግኘት ይችላሉ።
በOpenAI የቴክኒክ ቡድን አባል የሆነው አሮን ፍሪል፣ ብዙውን ጊዜ ብልሽት ሲከሰት የምላሽ ሥራውን ይመራል። ለብልሽቱ ምላሽ ለመስጠት የSlack ቻናል ይከፍታል። ከዚያም Codexን ወደ ችግሩ በመምራት፣ ክትትል እንዲያደርግ፣ እንዲመረምርና ጥያቄዎች ሲመጡ እንዲመልስ ይጠይቀዋል። «ማንኛውም ብልሽት ሲከሰት፣ ችግሩ ሊጀምርባቸው የሚችሉ ብዙ ደረጃዎች ይኖራሉ። በዚያ ቻናል ውስጥ ያሉት ሰዎች ዋነኛ ሥራም ትክክለኛውን ፍንጭ ከትክክለኛው የመረጃ ክምር ውስጥ ማውጣት ነው» ይላል። «Ultrafastን በመጠቀም፣ እነዚያን ሁሉ የመረጃ ክምሮች በአንድ ጊዜ መፈተሽና ለብልሽቶች እጅግ በፈጠነ ሁኔታ ምላሽ መስጠት እችላለሁ።»
የቴክኒክ ቡድን አባልና የዳታ ማዕከል ደህንነት አርክቴክት የሆነው ኤጄ ትርቦዬቪች እንደሚለው፣ የደህንነት ችግሮችን በሚመረምሩበት ጊዜ የተዋቀረና ያልተዋቀረ መረጃን መሰብሰብ፣ ወደ ወጥ ቅርጽ ማምጣትና ውሳኔ ለመስጠት የሚያስፈልገውን ዐውድ ማቅረብ ከአንድ እስከ ሁለት ሰዓት ይወስድ ነበር። «አሁን ይህ ከ10 እስከ 15 ደቂቃ ውስጥ ይከናወናል» ይላል። «አንዳንድ ጊዜም ምንም ያህል ሳይዘገይ ወዲያውኑ ይጠናቀቃል።»
አዳም ፔሪና ሳያን ሲሶዲያ ሁለቱም በዋናው የወኪል ቡድን ውስጥ ይሠራሉ። Codex እርምጃዎችን እንዲወስድ፣ ትዕዛዞችን እንዲያስኬድና መሣሪያዎችን እንዲጠቀም የሚያስችለውን ኮድ ይገነባሉ። Ultrafast የደህንነት ችግሮች ሲከሰቱ የሚሠሩበትን መንገድ ለውጦታል። «ቀደም ሲል Codexን አንድ ነገር እንዲመረምር እጠይቀውና፣ በዚያው ጊዜ እኔም ራሴ ምርመራውን እጀምር ነበር። ቁጭ ብዬ ለመጠበቅ የሚያስችለኝን ያህል ፈጣን እንዳልሆነ አውቅ ነበርና» ይላል አዳም። «አሁን በUltrafast፣ Codex በቂ ፍጥነት ስላለው ትኩረቴን ከመከፋፈል ይልቅ በአንድ ነገር ላይ አተኩሬ መቀጠል እችላለሁ።»
ሳያን Ultrafast ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ፈጣን መልሶችን እንዲያገኝ ማስቻሉን ያደንቃል፦ «ብልሽት ሲከሰት የስርዓት ምዝግቦችን ከመፈተሽ ባሻገር፣ Codexን Slack ውስጥ ለመፈለግ እጠቀምበታለሁ። አጠራጣሪ የሆኑ ለውጦች ተጠቅሰው እንደሆነ ወይም በሌሎች የSlack ውይይቶች ሰዎች ስለ ተመሳሳይ ምልክቶች እያወሩ እንደሆነ አያለሁ» ይላል።
ሌላው የቴክኒክ ቡድን አባል ጄፍ ኒዩ፣ በAI መልስ ማግኘት ከ30 ሰከንድ በላይ ከወሰደ፣ Slackን እንደሚያይ ወይም ከሥራ ባልደረባው ጋር እንደሚያወራ ይናገራል። አሁን ግን በUltrafast፣ ለአብዛኛው ሥራው ከዚያ ባነሰ ጊዜ ምላሽ ያገኛል። ቀደም ሲል Codexን ጥያቄ ይጠይቅና፣ እሱ እያሰበ ሳለ ወደ ሌላ ሥራ ይዞር ነበር። ሲመለስም የሃሳቡ ቅደም ተከተል ተቋርጦበት ያገኘው ነበር። አሁን ያ ውይይት ያለ መዘግየት ይካሄዳል፤ ይህም እየሠራው ባለው ሥራ ላይ ትኩረቱን እንዲያቆይ ይረዳዋል።
Ultrafast ያለውን ኮድ እንደገና ለማዋቀር የሚወስደውን ጊዜ ስለሚቀንስ፣ ጄፍ ሰፊ የኮድ መዋቅር ማሻሻያዎችን ለመሥራትም የበለጠ ፈቃደኛ ሆኗል። «ከዚህ በፊት ተከማችተው የቀሩ የቴክኒክ ማሻሻያ ሥራዎችን ማከናወን አሁን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቀላል ሆኗል» ይላል። «ኮድ ለመጻፍ ብዙ ወጪ አይጠይቅም፣ አሁን ደግሞ እጅግ በፍጥነት ይዘጋጃል። ብዙ ወጪ ይጠይቅ የነበረ የኮድ መዋቅር ማሻሻያ፣ አሁን በቅጽበት ማለት ይቻላል ይጠናቀቃል።»
አዳም ከCodex ጋር ቀጣይ ውይይት ያደርጋል፤ ይህንንም የሥራ አስተባባሪዬ ብሎ ይጠራዋል። በየማለዳው ምን ስብሰባዎች እንዳሉበትና ለየትኞቹ መልዕክቶች ምላሽ መስጠት ረስቶ ሊሆን እንደሚችል ይነግረዋል። «ያንን ማጠቃለያ ለመጻፍ መረጃውን ሁሉ አስቀድሞ አይቶታል። ስለዚህ ተከታይ ጥያቄ ስጠይቀው፣ ተጨማሪ መረጃ ለማምጣት አይዘገይም» ይላል። «እውነተኛ የሥራ አስተባባሪን እንደምጠይቀው ሁሉ፣ በዚያው ውይይት ውስጥ ጥያቄዎችን መጠየቅ መቀጠል እችላለሁ።»
ሳያን በአሳሽ ውስጥ በእጅ የሚሠሩ አሰልቺ ሥራዎችን፣ ለምሳሌ ቅጾችን መሙላትን፣ ለማከናወን Codexን ይጠቀማል። ከዚህ በፊት በጣም አዝጋሚ ስለነበር ለዚህ ሥራ ከመጠቀም ይቆጠብ ነበር። «አሳሽ ይከፍትና ለአምስት ሰከንድ ያስብ ነበር፤ አንድ ነገር ጠቅ ያደርግና እንደገና ይቆይ ነበር» ይላል። የቅርብ ጊዜዎቹ ሞዴሎች ኮምፒውተርን የመጠቀም ችሎታቸው በመሻሻሉ፣ ያንን ሥራ ለCodex ለመተው አሁን የበለጠ እምነት አለው። «አሁን በአሳሹ ውስጥ ጠቅ እያደረገ እንዲሠራ ያለ ስጋት እተወዋለሁ። ራሴ ባለመሥራቴ ጊዜ የማላጣበትን ያህል ፈጣን ነው።»
ለብልሽቶች ምላሽ በመስጠት፣ የዕለት ሥራን በማቀድና የኮድ መዋቅርን በማሻሻል ሥራዎች፣ Ultrafast የOpenAI ቴክኒክ ባለሙያዎች ጥያቄዎቻቸው በሚመጡበት ፍጥነት ከCodex ጋር እንዲሠሩ ያስችላቸዋል። ባገኙት መልስ ላይ ተከታይ ጥያቄ መጠየቅ፣ ሌላ አቀራረብ መሞከርና የሃሳባቸው ቅደም ተከተል ሳይቋረጥ ሥራቸውን መቀጠል ይችላሉ። የመጠበቂያ ጊዜው ማጠሩ፣ ለመሥራት ፈቃደኛ የሚሆኑባቸውን ተግባራትም ይቀይራል፤ ለሌላ ጊዜ ካስተላለፉት የኮድ መዋቅር ማሻሻያ ጀምሮ፣ አሁን በመጨረሻ ለCodex መስጠቱ ጠቃሚ እስከሆነው መደበኛ ሥራ ድረስ።
- Codex
- 2026


